1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቄለም ወለጋ በታጣቂዎች ደርሷል ስለተባለ ግድያና አፈና

ማክሰኞ፣ የካቲት 1 2014

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን መንግስት በአሸባሪነት በፈረጀው ኦነግ-ሸኔ ወይም እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ለወራት ተቆጣጥሮት በነበረው ጊዳሚ ወረዳ በንጹሃን ላይ ያደረሰው ግድያ ገና አለመጣራቱን የዞኑ ፀጥታ አስተዳደር ለዶይቼ ቬለ ገለጸ።

https://p.dw.com/p/46i23
Äthiopien | Straßenszene in Mendi
ምስል Negassa Deslagen/DW

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን መንግስት በአሸባሪነት በፈረጀው ኦነግ-ሸኔ ወይም እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ለወራት ተቆጣጥሮት በነበረው ጊዳሚ ወረዳ በንጹሃን ላይ ያደረሰው ግድያ ገና አለመጣራቱን የዞኑ ፀጥታ አስተዳደር ለዶይቼ ቬለ ገለጸ።

የፀጥታ አስተዳደር ኃላፊው አቶ ተሰማ ዋሪዮ እንደሚሉት ታጣቂ ቡድኑ አግቶ የወሰዳቸው የወረዳው ፀጥታ እና አስተዳደር ኃላፊዎችና ሰራተኞች በህይወት ይኑሩ አይኑሩ ገና ማረጋገጥ አለመቻሉንም አስታውቀዋል።

ኃላፊው ለወራት በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበረች ጊዳሚ ወረዳ አሁን ላይ ወደ መንግስት አስተዳደር መመለሷንም ነው ያመለከቱት። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በትናንትናው እለት የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳደር ተወካይና የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብሣ በሻን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሸኔ በሚል ስም በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ጦር 168 ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል።

ዘግናኝ በተባለ መንገድ ተገድለዋል ከተባሉት ንጹሃን ዜጎችም 81ዱ በወረዳው በተለያዩ ቦታዎች መገደላቸውን፤ እንዲሁም በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው አንድ ቦታ የተገኙ 87 ሰዎችን ባጠቃላይም 168 ንጹሐን መገደላቸውን ነው ዘገባው ያወሳው። ዶይቼ ቬለ ስለተፈጸመው ግድያ የአይን እማኞች እና የሟቾች ቤተሰቦችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም፤ የቄለም ወለጋ ዞን ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ተሰማ ዋሪዮን አነጋግሯቸዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚሉት ለወራት በታጣቂዎች ስር የነበረው ጊዳሚ ወረዳን ሰሞኑን ወደ መንግስት አስተዳደር መመለስ ቢቻልም የወረዳው አመራሮች ተወስደው የት እንዳሉ ገና አለማጋገጣቸውን አብራርተዋል፡፡ 

የወረዳው አስተዳዳሪዎች እና የፀጥታ ሰራተኞች ታግተው ስለመወሰዳቸው ከታገቱት ውስጥ አምልጦ ከወጣ ሰው ማረጋገጥ መቻሉን ያስረዱን ኃላፊው ቀጥለን የአጋቹን ማንነት ጠየቅናቸው፡፡ እስካሁን የሚታወቀው ታግተው በታጣቂዎች የተወሰዱት የመንግሰት መዋቅር በተለያዩ ኃላፊነቶች የሚሰሩ መሆናቸው ብቻ ነውም ብለዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳን የሚታዋስነውና ለወራት በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበረችው የቄለም ወለጋዋ ጊዳሚ ወረዳ ከዞኑ ዋና ከተማ ደምቢዶሎ 160 ኪ.ሜ. ገዳማ እንደምትርቅም ተገልጿል፡፡ ተፈጽሟል ስለተባለው ጅምላ ጭፍጨፋ እና ግድያው ለማውቅ ገና አለመቻሉንና የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች የሚያደርጉትን ኦፕሬሽን መቀጠላቸውንም አቶ ተሰማ አብራርተዋል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ