የሱዳን ጦርነት ባጭር ጊዜ ውስጥ በሰፊው በመሰራጨትና በርካታ ሚሊዮንችም በማፈናቀልና እንዲሰደዱ በማድረግ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሁኗል። ሆኖም ግን፤ ብዙ ሽፋን እንዳልተሰጠውና ጦርነቱን ለማስቆምም አቅሙና ችሎታው ካላቸው ወገኖች ብዙም ፍላጎት እንዳልታየ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት። ሁለቱም ወገኖች ያለ ሌላ ሦስተኛ ወገን ድጋፍ ጦረነቱን ለማስጀመርም ሆነ ለማስቀጠል አይችሉም ነበር የሚሉት እነዚሁ ታዛቢዎች፤ የቅርብም ሆነ የሩቅ ግን አቅሙ ያላቸው መንግሥታት ይልቁንም ሁለቱንም ወይም ከሁለቱ አንዱን በመርዳት ለሱዳን መውደምና ለሱዳንውያን እልቂት አስተዋጾ አድርገዋል በማለት ይወቅሳሉ። እየወደመች ካለችው ሱዳንና በጦርነትና ርሀብ እያለቁ ካሉት ሱዳኖች ይልቅ፤ ለአውሮጳውያኑ ዋናው አሳስቢው ጉዳይ ርሀብ ጦርነቱን ሸሽተው ለስደት መንገድ የገቡት ሱዳናውያን ወደ አውሮጳ እንዳያመሩ መሆኑን የአውሮጳ ሕብረት በቅርቡ ለግብጽ የለገሰውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም ለአብነት ይጠቅሳሉ እነዚሁ ታዛቢዎች።