1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣የቅዱሱ ምድር መበቃቀል፣የአሜሪካ ዲፕሎማሲ

ሰኞ፣ ጥር 22 2015

ከጆርጅ ሲ ማርሻል እስከ ጆን ፎስተር ዳላስ፣ ከሔንሪ ኪንሲንጀር እስከ ማድሊን ኦል ብራይት፣ ከሒላሪ ክሊተን እስከ ማይክ ፖምፒዮ የተቀያየሩት የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች መካከለኛዉ ምስራቅን ተመላልሰዉበታል።ሰላም ለማስፈን በወርቃማ ቃላትና አረፍተ ነገሮች ቃል ገብተዋል።ብሊንከንም ደገሙት።ሰላም ግን እዚያ ምድር የለም

https://p.dw.com/p/4MtCL
Israel Mehrere Tote bei Schießerei in Ost-Jerusalem
ምስል Ahmad Gharabli/AFP

እስራኤሎችም ፍልስጤሞችም እኩል ተገደሉ

 

ፍሎስጤሞች የዘመኑ ዓለም ያፈራዉን የዉጊያ ዕዉቀት ከነምርጥ ጦር መሳሪያዉ በታጠቀዉ የእስራኤል ጦር ኃይል፣ እስራኤሎች «አሸባሪ» ባሉት ታጣቂ እኩል ተገደሉ።የሟች ወላጅ-ወዳጅ ዘመዶችም ያዉ እንደ ሰዉ እኩል አለቀሱ።የእስራኤል ባለስልጣናት እንደ ጠንካራ ሐገር መሪ፣ለብቀላ ሲዝቱ ግን የፍልስጤሞች እንደ ሐገር አልባዎች ተወካይ ለአቤቱታ ተዘጋጁ።ሐዘን፣ ለቅሶ፣ ዛቻ አቤቱታዉ በናረበት መሐል የእስራኤል የቅርብ አጋርና ወዳጅ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እየሩሳሌም ገቡ።ከዚያስ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
                                     
የእስራኤል ዕዉቅ ፖለቲከኛ ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈዉ ታሕሳስ ዳግም የሐገሪቱን የጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን እንደያዙ ሲሰፋ የመካከለኛዉ ምስራቅ፣ ሲጠብ የእስራኤልና የፍልስጤም ግንኙነት የሚበየነዉ ኔታንያሁና ባይደን በሚኖራቸዉ ወዳጅነት ልክ ነዉ የሚለዉ አስተያየት ሲራገብ ነበር።
እርግጥ ነዉ ባይደን-ኔታንያሁ ኖሩም አልኖሩ የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤል ግንኙነት እስራኤል እንደ ሐገር ከተመሰረተች ጀምሮ የፀና፣ አንዳዴ አንድም-ሁለትም እስኪመስሉ ድረስ የተቀራረበ መሆኑ አያጠራጥርም።
የሁለቱ መሪዎች መግባባት ደግሞ፣ የቀድሞዉና አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለጆ ባይደን በዓለ ሲመት ባስተላለፉት መልዕክት ነባሩን ግንኙነት ይበልጥ አደድሮ የእስራኤል-አረቦችን፣የእስራኤል ፍልስጤሞችን የዘመናት ጠብ አንድም አለዝቦ ሁለትም አንሮ ለተረኞች ለመልቀቅ ወሳኝ ነዉ። 
                                        
«ፕሬዝደንት ባይደን፣ እርስዎና እኔ ብዙ አስርታት ያስቆጠረ የሞቀ የግል ወዳጅነት አለን።የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ትብብር ለማጠናከር፣በእስራኤልና በዓረቡ ዓለም የተጀመረዉን ሰላም ለማስፋፋትና የጋራ ፈተናዎችን ከነዚህ መሐል ዋናዉ ኢራን የደቀነችዉን ስጋት ለማስወገድ አብሬዎት ለመስራት ጥግጁ ነኝ።»
ኔታንያሁ ከባይደን ጋር ለመስራት ዝግጅታቸዉን ሳይጨርሱ ከስልጣን ወርደዉ ነበር።ግን ባለፈዉ ታሕሳስ እንደገና ተመለሱ።የኔታንያሁ የቀድሞ አማካሪ ማርክ ሬጊቭ በዚያዉ ሰሞን ባሳተሙት መጣጥፍ እንዳሉት የባይደን-ኔታንያሁ ወዳጅነት 40 ዘመን ያስቆጠረ ነዉ።
በ1982 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባይደን ወጣት ሴናተር፤ ኔታንያሁ ጀማሪ ዲፕሎማት በነበሩበት ዘመን የተጀመረዉ ትዉዉቅ ዳብሮ በግል እስከ መገባበዝ፣ አንዱ ሌላዉን በመጀመሪያ ስም እስከ መጠራራት ዳብሯል።
ይሁንና ወቅቱ ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬን ሰበብና ዩክሬን ላይ ከሩሲያ ጋር በገጠመችዉ ጦርነት-አንድ፣ ከኢራን ጋር በገባችዉ ቁርቁስ-ሁለት ፣ከቻይና ጋር በምታደርገዉ  ሽኩቻ-ሶስት፣ምክንያት የጠላቶችዋን ቁጥር ለመቀነስ የምትዳክርበት ጊዜ ነዉ።ፕሬዝደንት ባይደን በቅርቡ የተጋለጠባቸዉ ሚስጥራዊ ሰነድ በመደበቅ ቅሌት ሰበብ ከሪፐብሊካን ተቀናቃኞቻቸዉ የተቀሰቀሰባቸዉን ተቃዉሞ ለማርገብ እየተወከቡም ነዉ።
በዚሕ መሐል ወትሮም አክራሪ የሚባሉት ኔታንያሁ ከሳቸዉ የባሱ አክራሪ፣ ፅንፈኛ፣ፖለቲከኞችን ያካተተ ካቢኔ መስርተዉ እንደ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ብቅ ማለታቸዉ ላዛር ቤርማን የተባሉ ተንታኝ እንደፀፉት ለ80 ዓመቱ አዛዉንት ፕሬዝደንትና ለሚመሩት አስተዳደር ከፍተኛ «ራስ ምታት» ነዉ።
ባይደን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከንን ወደ በካይሮ በኩል ወደ እየሩሳሌም የላኩት በእስራኤል ታሪክ እጅግ-ቀኝ አክራሪ የሚባለዉን የኔታንያሁን መንግስት ሥራና አሰራርን ለማረቅ፣የሁለቱን ሐገራት ነባር ግንኙነት ለማጠናከር ወይም የባይደን-ኔታንያሁን የቅርብ ወዳጁነትን ለማረጋገጥ መሆኑ አላነገረም።
ብሊንከን ከዋሽግተን ለመነሳት መረጃቸዉን ሲሰንዱ ባለፈዉ ሐሙስ ግን የእስራኤል ጦር፣ እስራኤል በኃይል በያዘችዉ ምዕራባዊ ዮርዳኖ ወንዝ ዳርቻ ጄኒን የሚገኘዉን የፍልስጤም ስደተኞች ጣቢያን ወርሮ 10 ፍልስጤማዉያንን ገደለ።ከሟቾቹ አንዷ የ61 ዓመት አሮጊት ናቸዉ።ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ለቅሶ፣ ቀብርና ፀሎት አረበበ።
ዋሽግተን።የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ረዳት ቃል አቀባይ ቬንዳንት ፓቴል አሸባሪዎችን አወገዙ፣ሰላማዊ ሰዎች በመሞታቸዉ ሐዘናቸዉን ገለጡ፣ገዳዮችን ግን-----
«እስራኤልና የፍልስጤም መስተዳድር የገጠማቸዉን ከፍተኛ የፀጥታ ፈተና እንገነዘባለን።በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱና ለማጥቃት የሚያቅዱ አሸባሪ ቡድናትን እናወግዛለን።ሰላማዊ ሰዎች በመሞታቸዉ እናዝናለን።»
የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ባለስልጣናት ዜጎቻቸዉን አይደለም የራሳቸዉንም ደሕንነት  ሊጠብቁ አይችሉም።ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን የፀጥታ ጥበቃ ትብብር ለማቋረጥና ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አቤት እንደሚሉ ለማስታወቅ ግን አልሰነፉም።የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር የእየሩሳሌም አገረገዢ አማካሪ ማአሩፍ አል ሪፊ-አርብ።
«የፀጥታ ጥበቃ ማስተባበሩን በተመለከተ፣አጠቃላይ ርምጃ  ለመዉሰድ (ለማቋረጥ)ወስነናል ሁሉም የፍልስጤም ሕዝብ በሙሉ ዉሳኔዉን ይደግፋል።ይሕ ግዛታችንን በኃይል የመያዝ እርምጃ ተገቢዉን ቅጣት ያገኝ ጠንድ መሪዎቻችን ይሕን ወንጀል ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አቤት ማለት አለባቸዉ።»
ፍልስጤሞች ለፍርድ ቤት አቤት ለማለት መዘጋጀታቸዉን ከተከሳሽዋ እስራኤል ቀድማ የተቃወመችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።ጋጤኛዉ ጠየቀ «ታዲያ ፍልስጤሞች ደሕንነታቸዉን ለማስከበር የት ይሂዱ» እያለ።
«እሺ ፍልስጤሞች ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት፣ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ ለሌላ አለም አቀፍ ድርጅት  አቤት ማለታቸዉን ካልተቀበላችሁ፣ የት ይሂዱ ታዲያ?»
የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ቬንዳንት ፓቴል ግልፅ መልስ የላቸዉም።ግን የሚሉት አላጡም።
«እኛ የምናነዉ ይህ ጉዳይ እስራኤሎችና የፍልስጤም ባለስልጣናት መደራደር አለባቸዉ።እስራኤልና ፍልስጤም መስተዳድር ሁኔታዉን የሚያባብስ ርምጃ እንዳይወስዱ ማድረግ እንዳለባቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ታምናለች።»
አርብ ፍልስጤሞች ሙቶቻቸዉን ሲቀብሩ፣ የዩናይትድ ስትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ወደ ካይሮ ለመብረር ሲነሱ፣የእየሩሳሌም ምኩራብ በተኩስ ተናወጠ።አንድ ፍልስጤማዊ ታጣቂ በከፈተዉ ተኩስ 7 እስራኤላዉያን ተገደሉ።እየሩሳሌም ለቅሶ፣ፀሎትና ቀብር።

የእስራኤል ጦር ያወደመዉ የፍልስጤሞች መንደር
የእስራኤል ጦር ያወደመዉ የፍልስጤሞች መንደርምስል Raneen Sawafta/REUTERS
አንድ ፍልስጤማዉ በከፈተዉ ተኩስ 7 ተገድለዋል
አንድ ፍልስጤማዉ በከፈተዉ ተኩስ 7 ተገድለዋልምስል AHMAD GHARABLI/AFP
ጀኒን የተገደሉት ፍልስጤማዉያን የቀብር ሥርዓት
ጀኒን የተገደሉት ፍልስጤማዉያን የቀብር ሥርዓትምስል Ahmed/Ibrahim/APA/IMAGO

                              
ዋሽግተን ዉግዘትና ዛቻ፣ እንደገና  አቀባይ ቬንዳንት ፓቴል።

«ይሕን የአሸባሪ የሚመስል ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን።የእስራኤልን ፀጥታ ለማስከበር ያለን ቁርጠኝነት ከብረት የጠነከረ ነዉ።»
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ከ1948 ጀምሮ ከዋሽግተን ለቴል አቪቭ፣ ኋላ ለእየሩሳሌም የሚንቆረቆረዉ የፖለቲካ፣ዲፕሎማሲ፣የገንዘብ ጦር መሳሪያ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
መካከለኛዉ ምስራቅ ግን የጦር ኃይል ጥንካሬ፣ዓለምን የማስገበር ጉልበት፣ የዲፕሎማሲ-ፖለቲካ ብልጠት ለሰላም አልበጀዉም።የዳዊት አስተምሕሮ፣ የሰለሞን ጥበብ፣ የእየሱስ ሰባካ፣ የመሐመድ ዱዓ፣ የናቡከደና ፆር ኃይል፣ የናስር ቁርጠኝነት፣የቤን ጎሪዮን ፅናት አልገራዉም።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ግን አሁንም አብነቱ ፀሎት-ምሕላ ድርድር-ዉይይት  ነዉ ባይ ናቸዉ።
«ዕለት በዕለት እየባሰ የመጣዉ ግድያ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ብልጭ ድርግም የምትለዉን መተማመን ጨርሶ ከማጥፋት በስተቀር የተከረዉ ነገር የለም።ሁለቱ መንግስታትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሙሉ ምንም ሳይዘገዩ ሌላ ድርድር ጨምሮ እዉነተኛ ሰላም ለማስፈን ከልብ እንዲጥሩና ሌላ መንገድ እንዲፈልጉ እማፀናለሁ።ለሟች እህት ወንድሞቻችን እንፀልይ።»
ጥሪ፣ተማፅኖዉን እስካሁን የሰማ እንጂ ከልብ የጣፈዉ የለም።የእስራኤል ጠንካራ የብቀላ ርምጃ እንደ ኦሪቱ «አይን-ላጠፋ ዓይን» ከሚለዉም የከፋ ነዉ።እስራኤላዉያኑን ገደለ የተባለዉ የ21ድ ዓመቱ ፍልስጤማዊ ወዲያዉ ተገድሏል።የገዳይ ቤተሰቦች ቤታቸዉ ታሽጎ ሜዳ ላይ ፈስሰዋል።
የእስራኤል ፖሊስ ትናንት እንዳስታወቀዉ ከገዳዩ ጋር በአባሪ-ተባባሪነት የጠረጠራቸዉን 42 ፍልስጤማዉያን አስሯል።ስልጣን በያዙ በሳምቱ የሙስሊሞችን ቅዱስ ስፍራ የአል-አቅሳ መስጊድን ቅጥር ግቢ በመርገጣቸዉ አዲስ ቁጣና ብጥብጥ የቀሰቀሱት ፅንፈኛዉ የእስራኤል የፀጥታ ሚንስትር ኢታማር ቤን-ግቪር ደግሞ ሲቪል የእስራኤል ዜጎችን ጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ ቃል ገብተዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸዉ ሊጎዳን ለሞከረ ሁሉ ምሕረት የለንም አሉ-ዕሁድ።
 «አፀፋችን ጠንካራ፣ ቅፅበታዊና ቀጥተኛ  ነዉ።ሊጎዱን የሚሞክሩ ሁሉና ማንኛዉም ተባባሪዎቻቸዉን እንጎዳለን።»
የናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ካይሮ፤እየሩሳሌምና ረመላሕን ለመጎብኘት ያቀዱት ከወራት በፊት ነበር።የጉብኝቱ አላማ ብዙ ነዉ።ሩሲያን ለማግለልና ለማሳጣት፣የዩናይትድ ስቴትስና የግብፅን ትብብር ለማጠናከር፣ ዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ጥብቅ ወዳጅነት ለማረጋገጥ፣ ምናልባት የባይደን-ኔታንያሁን ወዳጅነት ለማረጋገጥ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በምትመራዉ ዓለም ተስፋ ያጡት ግን በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ የሚኖሩት የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር መሪዎች ወደ ሞስኮና ቴሕራን እንዳያማትሩ ለማግባባት እየተባለ የሚዘረዘር በርካታ ነዉ።
ብሊንከን ዛሬ ቤን-ጎሮዮን አዉሮፕላን ማረፊያ-እስራኤል፣ ሲደርሱ እንዳሉት ግን በፊት ያቀዱት ሁሉ ቅጥያ ሆኖ ዋና ተልዕኳቸዉ እሳት ማጥፋት ነዉ።
«ዉጥረትን ከማቀጣጠል ይልቅ ለማብረድ የሚጠቅሙ ርምጃዎችን መዉሰድ የሁሉም ኃላፊነት ነዉ።ሰዎች በየማሕበረሰባቸዉ፣ በየቤታቸዉ፣በየቤተ-ዕምነታቸዉ ዉስጥ ሲሆኑ የሚፈሩበት ጊዜ እንዳይኖር መጣር ነዉ።የብዙ እስራኤሎችን፣የብዙ ፍልስጤሞችን ሕይወት ያጠፋዉን፣ እየከፋ የመጣዉን ሁከት ማስወገድ የሚቻለዉ ይሕን በማድረግ ብቻ ነዉ።እስራኤልና ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በምቆይበት ጊዜ ለማገኛቸዉ ሁሉ የማስተላልፈዉ መልዕክት ይሕንን ነዉ።»
እስራኤል ከተመሰረተች ከ1948 ጀምሮ 24 የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ተፈራርቀዋል።ከጆርጅ ሲ ማርሻል እስከ ጆን ፎስተር ዳላስ፣ ከሔንሪ ኪንሲንጀር እስከ ማድሊን ኦል ብራይት፣ ከሒላሪ ክሊተን እስከ ማይክ ፖምፒዮ የተቀያየሩት የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች መካከለኛዉ ምስራቅን ተመላልሰዉበታል።ሰላም ለማስፈን በወርቃማ ቃላትና አረፍተ ነገሮች ቃል ገብተዋል።ብሊንከንም ደገሙት።ሰላም ግን እዚያ ምድር የለም።

ከግራ ወደ ቀኝ ብሊንከንና ኔታንያሁ
ከግራ ወደ ቀኝ ብሊንከንና ኔታንያሁምስል Ronaldo Schemidt via REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ